Jump to content

ዓፄ ሱሰኒዮስ

ከውክፔዲያ
(ከሱስኒዮስ የተዛወረ)

==

ዓፄ ሱስኒዮስ
ማሪያም ግምብ የአፄ ሱስኒዮስ ቤተ መንግስት በጎርጎራ
ማሪያም ግምብ የአፄ ሱስኒዮስ ቤተ መንግስት በጎርጎራ
ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ
ግዛት ከ1606 እስከ 1632 እ.ኤ.አ.
በዓለ ንግሥ 1608 እ.ኤ.አ.
ቀዳሚ ዓፄ ያዕቆብ
ተከታይ አፄ ፋሲለደስ
ልጆች አፄ ፋሲለደስ
ሙሉ ስም መልአክ ሰገድ (የዙፋን ስም)
ሥርወ-መንግሥት ሰሎሞን
አባት አቤቶ ፋሲለደስ
እናት ወ/ሮ ሐመልማለ-ወርቅ
የተወለዱት 1572 እ.ኤ.አ.
የሞቱት 1632 እ.ኤ.አ.
ሀይማኖት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ፣ ከ1622 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ የሮማ ካቶሊክ ክርስትና

==


ዓፄ ሱስኒዩስ በዙፋን ስማቸው "መልአክ ሰገድ" ተብለው ሲታወቁ በ1572 ተወልደው በ1632 (እ.ኤ.አ)አርፈዋል። ከ1606–1632 እ.ኤ.አ. የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩ ሲሆን፣ አባታቸው የአፄ ልብነ ድንግል የልጅ ልጅ የሆኑት አቤቶ ፋሲለደስ እና ልጃቸው ደግሞ ዓፄ ፋሲለደስ ነበሩ። እናታቸው ወይዘሮ ሐመልማለ-ወርቅ የተሰኙ የጎጃም አስተዳዳሪ ልጅ ነበሩ።

በሱሰንዮስ ዘመን የነበረው የጀስዩት ሚስዩን አልሜዳ ሱሰንዩስ "ረጅም፣ ወንዳወንድ፣ ትላልቅ አይኖች ያሉት፣ አፍንጫው ቀጥ ያለና ጢሙም በጥንቃቄ የተከረከመ ነው" ካለ በኋላ አለባበሱን ሲገልፅ " [በጊዜው የአውሮጳውያን ፋሽን የነበረውን አይነት] እስከ ጉልበቱ የሚደርስ ከደማቅ ቀይ ሐር የተሰራ በፍታ በስስ ጥብቅ ያለ ሱሪ እና በትላልቅ ወርቅ ያጌጠ ቀበቶ ለብሶ ከላዩ ላይ በተለያየ ቅርጻቅርጽ ያጌጠ ካባ ይደርባል። "[1]

የህይወት ታሪክ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሱሰኒዩስ የተወለደው የአህመድ ግራኝ ሰራዊት ከተሸነፈ በኋላ ሲሆን በዚህ ጊዜ የህዝብ ንቅናቄ ይታይ ነበር። የሱሰኒዮስ ዜና መዋዕል እንደሚያትተው በህፃንነቱ ከአባቱ ጋር ጎጃም ውስጥ ይኖሩበት የነበረው ከተማ በአንድ ተንቀሳቃሽ የኦሮሞ ቡድን ስር ወደቀ ፤ አባቱና ቀሪው የከተማው ሰው ሲገደል እሱ ግን ለአንድ አመት ከግማሽ በምርኮ ከኦሮሞው ቡድን መሪ ጋር ተቀመጠ። ከዚያ በኋላ የኦሮሞው ቡድን በዳሞትደጅ አዝማች አስቦ ጋር ጦርነት ለመግጠም ሞክሮ በመሸነፉ ወደአካባቢው ዋሻወች በመግባት ለመሸሸግ ሞከረ። የደጃአዝማች አስቦ ሰራዊት የተሸሸጉትን ቡድኖች አባላት እዋሻው ድረስ በመግባት ከነመሪያቸው በሰንሰለት አሰሩዋቸውና "ህጻኑን ሱሰኒዮስ ካመጣችሁ ትለቀቃላችሁ ካላመጣችሁ ግን ትገደላላችሁ" አላቸው። ሱሰኒዮስ በዚህ መንገድ ሲለቀቅ፣ ደጃች አስቦ ህጻኑን መንገዱ ለተባለ የአቤቶ ፋሲለደስ ወዳጅ በአደራ ሰጡት። መንገዱም የንግስት አድማስ ሞገሴ (የአፄ ሰርፀ ድንግል እናት) ቤተኛ ስለነበር ህጻኑ ከንግስቲቱ ዘንድ አደገ ። [2]

ወህኒና አጼ ያዕቆብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]
የሱሰኒዮስ ቤ/መንግስት በደንቀዝ (ከሩቁ)

በ1590ወቹ የአፄ ሰርፀ ድንግል ልጆች እድሜያቸው ገና ጨቅላ ስለነበር ፣ አጼው ፣ የወንድማቸውን ልጅ ዘድንግልን ለተተኪ ንጉስነት አጭተውት ነበር። ንግስት ማርያም ሰናና የወቅቱ መሳፍንት (ለምሳሌ ራስ አትናቲወስ) የ 7 ዓመት ህጻን የነበረው የሰርፀ ድንግል ልጅ ያዕቆብ እንዲነገስ የአባቱን ሃሳብ አስቀየሩ። ህጻኑም የነገሰበት ጊዜ ከ1597 እስከ 1603 ነበር። በዚህ ጊዜ የርስ በርስ ጦርነት እንዳይነሳ ለህጻኑ ስልጣን ተቀናቃኝ ሊሆን ይችላል የተባለውና በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈውን ዘድንግልን በግዞት ወደ ጣና ሃይቅ እንዲባረር አደረጉ። ሱሰኒዮስም ከዘድንግል ጋር አብሮ ከማደጉ በተጨማሪ ይዋደዱ ስለነበር ( እንዲሁም ልክ እንደ ዘድንግል ለያዕቆብ ስልጣን አስጊ ሆነ ስለተገኘ) በማምለጥ በጎጃምና ሸዋ ገዳማት እንዲሁም በኋላ ከተንቀሳቃሽ ኦሮሞወች ጋር ኑሮውን አደረገ። አብረውት ከነበሩት ኦሮሞወች ሠራዊት በመመልመል ሸዋ ውስጥ በተለይ ይፋትን፣ መርሃ ቤቴንና ቢዛሞን በጦርነት ተቆጣጠረ።

ወጣቱ ንጉስ ያዕቆብ የጊዜው መኳንንቶች ስልጣን ያለገደብ መሆኑን በመቃወም ስልጣናቸው እንዲገደብ በመሞከሩና በእድሜው ምክናያት በሱ ቦታ ሆኖ አገሪቱን የሚያስተዳድረውን ራስ አትናቲወስን ስልጣን መጋፋት ሲጀምር ከዘመኑ ባለስልጣኖች ጋር ጥል ገባ። በዚህ ጊዜ መኳንንቶቹ "ሃይማኖት የለሽ አረመኔ" እና "ጠንቋይ" ነው የሚል የፈጠራ ወሬ በንጉሱ ላይ በመንዛት በግዞት ከስልጣን እንዲባረርና በእንራያ በስደት እንዲኖር አደረጉት። አጼ ዘድንግልን በ 1603 የጉራጌው ራስዘስላሴ አቀነባባሪነት ንጉሰ ነገስት አደረጉት። ዘድንግል፣ ምንም እንኳ አይምሮው ብሩህ የነበረ መሪ ቢሆንም ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት በማዘንበሉ ምክንያት አመጽና ጦርነት ተነስቶበት በ1604 በላባርት ጦርነት ሞተ።

ዘድንግል ባለፈ ጊዜ ሱሰኒዮስ በምስራቅ ጎጃም በምተገኘው ጥንታዊቷ መርጡለማሪያም ቤ/ክርስቲያን የዙፋን አክሊል ደፋ (ህዳር 1604 እ.ኤ.አ)። ነገር ግን ራስ ዘስላሴና አንዳንድ መኳንንት ቀደምት የተባረረውን ንጉስ ያዕቆብን በመደገፍ አቋም ያዙ፣ እንዲሁም መልሰው አነገሱት ። በአንድ አገር ሁለት አጼ መኖር ስለማይችል፣ ሱሰኒዮስ፣ ራስዘስላሴን ጦርነት ገጥሞ ከማረካቸው በኋላ አጼ ያዕቆብን በ1607 ደቡብ ጎጃም ውስጥ የጎል ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ገጥሞ አሸነፈው። ከዚህ ጦርነት በኋላ ሱሰኒዮስ ብቸኛው የአገሪቱ መሪ ሆነ።

ራስ ዘስላሴም ከምርኮ በኋላ ሱሰኒዩስን ይደግፉ እንጂ ቆይተው፣ ንጉሱ ወደ ካቶሊክ ሃይማኖት በማድላቱ፣ መጣላታቸው አልቀረም ። በዚህ ምክንያት በምስራቅ ጎጃም በሚገኝው አምባ ጉዛምን ለእስር ተዳረጉ። አምባው ላይ አመት ከቆዩ በኋላ በማምለጥ በሽፍትነት እያሉ አንድ ገበሬ ገድሎ እራሳቸውን ለንጉሱ ሱሰኒዮስ እንደላከ ጄምስ ብሩስ ይተርካል። [3]

በደንቀዝ ተሰርቶ የነበረው የቤተመንግስቱ አቅድ

አሰምሳዮቹ አጼ ያዕቆቦች

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ጎል ጦርነት ጊዜ የአጼ ያዕቆብ ሰራዊት ሽንፈት ይድረስበት እንጂ የንጉሱ ሬሳ በጦር ሜዳው ስላልተገኘ በጦርነቱ መሞቱ አጠራጣሪ ሆነ። በዚህ ምክንያት ብዙ "አጼ ያዕቆብ እኔ ነኝ"የሚሉ የአመጽ መሪወች በሱሰኒዮስ ንግስና ዘመን ተነሱ። ለምሳሌ ሱሰኒዩስ ከነገሰ በኋላ በ1608 ደብረ ቢዘን (ያሁኑ ኤርትራ ) ውስጥ አጼ ያዕቆብ ነኝ የሚል ብዙ ተከታይ ያለው መሪ ተነሳ። ይህ አሰምሳይ ንጉስ ሁል ጊዜ ፊቱን ተሸፋፍኖ ነበር ሰው ፊት የሚቀርበው። ለዚህ እንግዳ ጸባዩም የሚሰጠው ምክንያት "በጦርነት ፊቴ ላይ ጠባሳና ቁስል ስለደረሰ ሰውን ላለማስቀየም" ነው ይል ነበር ።[4]ትግራይ ገዢ የነበረው ሰዕለ ክርስቶስ የአመጹን መነሳት በሰማ ጊዜ የራሱንና የፖርቱጋል ወታደሮችን አሰልፎ በአስመሳዩ ንጉስ ላይ ዘመተ፡፡ አመጸኛው ሶስት ጊዜ በጦርነት ቢሸነፍም ሳይማረክ በማምለጥ በሐማሴን ተራራወች ለመደበቅ ቻለ። [5]

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የስዕለ ክርስቶስ ሰራዊት ወደ ሰሜን መክተቱን የሰሙት የኦሮሞ ቡድኖች ትግራይን በመወረር ከፍተኛ ጉዳት አደረሱ [6] በዚህ ምክንያት ንጉሱ ወደ ትግራይ ለመሄድ መሰናዶ ጀመረ።[7] በመሃል ግን በርብ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ የመረዋ ኦሮሞ ተብለው የሚታወቁ ቡድኖች ገጥመው በመጀመሪያው ዙር ስላላሸነፈ ለሁለተኛ ጊዜ ሃይሉን አጠናክሮ በመግጠም አሸንፎ እንዲበታተኑ አደረገ። የተበተኑት መረዋወች ከሌሎች ኦሮሞወች ጋር ሃይላቸውን አጠናክረው በማበር ለብቀላ እንደገና ወደ በጌ ምድር ወረራ አደረጉ። በዚህ ጊዜ ሱሰኒዩስ ከቀኛዝማች ጁሊየስ እና ክፍለ ክርስቶስ ጋር በመሆን ጥር17፣ 1608 የእብናት ጦርነት ተብሎ በሚታወቀው ድል አድረጉ። ጀምስ ብሩስ፣ የነገስታቱን ዜና መዋዕል ዋቢ አድርጎ እንደዘገበ፣ በ እብናት ጦርነት ወቅት ከንጉሱ ወገን 400 ሲሞቱ ከወራሪወቹ ዘንድ 12000 ሞተዋል ይላል። [8]

የዚህ ጉዳይ በንዲህ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ባለ ድሉ ሱሰኒዮስ፣ ወደ ትግራይሊማሊሞገደል እና ዋልድባ አድርጎ አቀና። በዚያውም የንጉሰ ነገስትነቱን ማዕረግ ታህሳስ 18፣ 1608 በአክሱም አጸና።[9] በትግራይ ውስጥ ተነስቶ የነበረውንም አመጽና የኦሮሞ ቡድን ጥቃት በማሸነፍ ጸጥታ አሰፈነ። ይሁንና አሰመሳዩን ያዕቆብን ለመያዝ ያደረገው ጥረት ፍሬ ስላላፈራ ስራውን መልሶ ለወንድሙ ስዕለ ክርስቶስ ተወለትና ወደ ቤተ መንግስቱ ደንካዝ ተመለሰ። ትንሽ ቆይቶም በስዕለ ክርስቶስ ገፋፊነት ሁለት የአስመሳዩ ያዕቆብ ተከታዮች መሪያቸውን በመግድል አንገቱን ቆርጠው ለሱሰኒዩስ ላኩ። ስኮቱ ጄምስ ብሩስ እንደመዘገበ "የአስመሳዩ እራስ ስላልተሸፋፈነ፣ አሰመሳዩ ፊት ላይ ምንም ጠባሳ፣ ምንም ቁስል፣ ምንም ችግር እንደሌለ አስተዋልን። ይልቁኑ ይሸፋፈን የነበረው ከእውነተኛው ንጉስ ያዕቆብ ጋር ምንም ምሥሥል እንዳልነበረው ለመደበቅ እንደነበር ተገነዘብን" [10] በማለት የደብረ ቢዘኑ አጼ ያዕቆብ ታሪክ በንዲህ መልክ ተቋጨ።

ሱሰኒዮስና የካቶሊክ እምነት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ሱሰኒዮስ በርግጥ ረጅም ጊዜ አገሪቱን ይምራት እንጂ አስተዳደሩ የሚታወቀው የኢትዮጵያን መንግስት ሃይማኖት ከተዋህዶ ወደ ካቶሊክ በመቀየሩ ነው። ሱሰኒዮስ ካቶሊክ ሃይማኖትን የተቀበለበት ምክንያት በሁለት ምክንያት ነበር፦ አንደኛው ፔድሮ ፔዝ የተባለው የጀስዩት ሰባኪ ስላግባባው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከፖርቹጋል እና ስፔን ወታደራዊ ድጋፍ ለማግኘት ነበር። በ ታህሳስ 10፣1607 ለፖርቹጋሉ ንጉስ እና ጥቅምት 14 1607 ለ ሮማው ፓፓ በጻፈው ደብዳቤው (አሁን ድረስ ይገኛል) ወታደሮች እንደሚፈልግ ሲገልጽ ነገር ግን ሃይማኖቱን መቀየሩን በሁለቱም ደብዳቤወች አይገልጽም፤ ይልቁኑ በሁለቱም ደብዳቤወቹ ሙሉ ትጥቅ ያደርጉ የአውሮጳ ወታደሮች እንዲልኩለት ይጠይቃል። [11] የዚህም ጥያቄ መነሻው የማያቋርጥ አመጽ አንዴ በሃይማኖት፣ ሌላ ጊዜ በ"አሰምሳይ ያዕቆቦች" በተረፈም በተንቀሳቃሽ የኦሮሞ ቡድኖች ስለተነሳበት ነበር።

ሱሰኒዮስ ከመጀመሪያው ጀምሮ ለካቶሊኮች ብዙ እርዳት አድርጓል፣ ለምሳሌ በግዛቱ መጀምሪያ ለካቶሊክ ጀስዊቶችጎርጎራ ሰፋፊ መሬት ሰጥቷቸው ነበር። ቆይቶም በ1622 ፣ የነበሩትን ብዙ ሚስቶች (ከመጀመሪያየቱ ሚስቱ በቀር) በመፍታት፣ የካቶሊክ እምነት መቀበሉን በአደባባይ አስታወቀ። ሆኖም ግን ፔድሮ ፔዝ ይባል የነበረው ለዘብተኛው የካቶሊኩ ቄስ በበሽታ በመሞቱ ከስፔን አልፎንሶ ሜንዴስ የተባለ ጳጳስ በኢትዮጵያ ላይ ተሹሞ በ1624 መጣ። አዲሱ ጳጳስ በጣም ግትር፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል፣ ጠባብ አይምሮ የነበረውና መቻቻል የማያውቅ ነበር [12]። ቶሎ ብሎም የቅዳሜን ሰንበትነት ሻረ፣ ብዙ አጽዋማትንም አስወጣ፣ ከዚያም በህዝብ ፊት የሮማው ፓፓን የበላይነት በኢትዮጵያ ላይ አወጀ።[13] በዚህ ምክንያት አመጽ ተነሳ። የሱሰኒዩስ ወንድም የማነ ክርስቶስ፣ ጃንደረባው ክፍለ ዋህድጁሊየስ ሦስቱ ሆነው ሱሰኒዮስን ሊገድሉት ሞከሩ ግን ሱሰኒዮስ አመለጠ። መልሰውም ጦርነት ጎጃም ውስጥ ከፈቱበት ግን ተሸነፉ [14]

ሱሰንዮስ (ከግራ) ከፖርቹጋል ለተላከው አዲሱ የካቶሊክ ፓትሪያርክ ሜንዴዝ (ከቀኝ) አቀባበል ሲያደርግ

የሃይማኖት አመጽ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

በሃይማኖት የተነሳው አመጽ እየጨመረ እንጂ እየበረደ ሊሄድ አልቻለም። በተለይ በወንድሙ መልክዐ ክርስቶስ ይመራ የነበረው የላስታ አመጽ ሊሸነፍ አልቻለም። በ1629 ወደ 30 ሺ ወታደሮች አስከትሎ የላስታውን አመጽ ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀረ። እንዲያውም መሪ የነበረው የሚስቱ ወንድም ልጅ በጦርነቱ ተገደለ[15] ለሁለተኛ ጊዜ መልክዓ ክርስቶስን ለመግጠም ያደረገው ሙከራ ከሁሉ ሁሉ የራሱ ወታደሮች ወኔ መኮስመኑን አስገነዘበው። በዚህ ምክንያት የወታደሮቹን ወኔ ለመገንባት የሃይማኖት ነጻነት በመፍቀድ የ"ዕሮብን ጾም" እንዲጾሙ ፈቀደ። ይሁንና አሁንም እንደበፊቱ የመልዐከ ክርስቶስ ጦር ሊበገር አልቻለም። ሱሰኒዮስ ያለምንም ፍሬ ወደ ቤ/መንግስቱ ዳንካዝ ባዶ እጁን ተመለ።

ለሶስተኛ ዙር ጦር ለመግጠም በሚዘጋጅበት ጊዜ የሰራዊቱ ወኔ ከመዝቀጡ የተነሳ ለመዝመት እንደማይፈልጉ ተገነዘበ። ላስታ ውስጥ የሚካሄደው የማያባራ ጦርነት ምንም ለውጥ እንዳላመጣ፣ የአገሪቱን ግዛት እንደማይጨምር፣ የሚዋጉዋቸውም ሰወች ጠላት እንዳልሆኑና፣ በሃይማኖት ምክንያት የነበረው ሰቆቃ እንዲያቆም በልጁ በፋሲለደስ አድርገው ወታደሮቹ ምክንያታቸውን ገለጹለት። ሱሰንዮስም መልሶ በዚህ በሶስተኛው ዙር የላስታውን አመጽ ድል ካደረጉለት የቀደመውን የኢትዮጵያ ሃይማኖት እንደሚመልስ በልጁ ላከባቸው። [16]

የሱሰኒዮስን ቃል ኪዳን ገንዘብ በማድረግ ሰራዊቱ ወደ ላስታ ተመመ። በዚህ መካከል 25፣000 የሚሆኑ የመልክዐ ክርስቶስ ሰራዊት ላስታን ለቀው መሃል መንገድ ላይ ሊገናኙት ሰልፍ እንደጀመሩ መረጃ አገኘ። ሐምሌ 26፣ 1631 ሰራዊቶች ተገናኙ። በዚህ ጊዜ ሱሰኒዮስ ከጥቂት ፈረሰኞቹ ጋር በመሆን በድፍረት ቀደም ብለው የመጡትን የመልዐክ ክርስቶስ ወታደሮች በማጥቃት እግረኛው ሳይቀላቀላቸው አሽመደመዱት። በዚህ ጊዜ ሌላው የላስታ ሰራዊት በፍርሃት ተበተነ፣ የንጉሱም ፈረሰኛ ጦር ብዙውን ገደለ። በዚህ ሁኔታ አመጸኞቹ ሲሸነፉ መሪያቸው የንጉሱ ወንድም ግን በፈረሱ ፍጥነት ምክንያት ሊያመልጥ ቻለ። በሚቀጥለው ቀን አጼ ሱሰኒዮስ ከልጁ ፋሲለደስ ጋር ያለፈውን ቀን የጦር ውሎ ለመገምገም ወደሜዳ ወጡ። 8000 የሚሆኑ የመልክዐ ክርስቶስ ሰራዊት መሞታቸውን ባየ ጊዜ ፋሲለደስ ለአባቱ እንዲህ ሲል መናገሩን ጄምስ ብሮስ ያትታል ፡

እነዚህ በሜዳ ላይ ታርደው የምታያቸው ወይም አረመኔ ወይም መሃመዳውያን አይደሉም። ሞታቸውም ምንም ደስታ አያመጣም። ክርስቲያን እና የራስህ ሰወች ናቸው፣ አንዳንዶቹም የስጋ ዘመዶችህ። ምንም ጥቅም የማይገኝበት ይሄ ድል አይደለም! እነዚህን በገደልክ ቁጥር እራስክን በጎራዴ ወግተህ እንደገደልክ ቁጥር ነው። ስንት ሰው አረድክ? ስንት ተጨማሪ መግደል ተፈልጋህ? መዘባበቻ ሆንን እኮ! በአረመኔወቹና በአረቦች ሳይቀር የእናት አባታቸውን ሃይማኖት ትተው እርስ በርሳቸው የሚተላለቁ እየተባልን የሰው መሳለቂያ ሆንን።

[17]

የልጁ ወቀሳ ውሸት እንደሌለውና ድሉ በኢትዮጵያን ዘንድ የበለጠ መጠላትን እንጂ መፈቀርን እንዳላተረፈለት ተረዳ። [18]

በዳንካዙ የሱሰንዮስ ቤ/መንገስት የጭስ መውጫ ዲዛይን

የሃይማኖት ነጻነት

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

ከዚህ ድል በኋላ አመት ባልሞላ ጊዜ ስኔ 14፣ 1632 ካቶሊክ ሃይማኖትን የሚከተል መከተል እንደሚችል፣ ግን ያን ሃይማኖት ማንም በግድ መከተል እንደሌለበት ከቤተ መንግስቱ ደንቀዝ አዋጅ አሳወጀ። በዚህ ጊዜ የካቶሊክ ቤ/ክርስቲያን የአገሪቱ መንግስት ቤ/ክርስቲያን መሆኑ አከተመለት። [19]

ስልጣን ርክክብ

[ለማስተካከል | ኮድ አርም]

የሃይማኖት ነጻነትን ካወጀ በኋላ ሃገሪቱን የመምራት ሃይሉ እንደሌለው ሲገነዘብ ቀስ በቀስ ለልጁ ስልጣኑን አስረከበ። ሐምሌ 1632 ፋሲለደስ ንጉሰ ነገስት ሲሆን ሱሰንዮስ ሙሉ በሙሉ ከስልጣን ወረደ። ወዲያውም የማይደን በሽታ ሱሰንዮስን ያዘውና በተወለደ በ61 አመቱ እ.ኤ.አ መስከረም 7፣ 1632 ከዚህ አለም በሞት ተለየ። በትልቅ ክብርና ስነስርዓት ልጁ በተገኘበተ በ ገነተ እየሱስ ቤ/ክርስቲያን ተቀበረ። [20]

[1]
  1. ^ (እንግሊዝኛ) C.F. Beckingham and G.W.B. Huntingford, Some Records of Ethiopia, 1593-1646 (London: Hakluyt Society, 1954), p. 189. Beckingham and Huntingford gloss capelhar as a "kind of short mantle of Moorish origin."
  2. ^ የሱሰኒዮስ ዜና መዋዕል። ምዕራፍ 1 (Chronicle of Susenyos)
  3. ^ (እንግሊዝኛ) James Bruce, Travels to Discover the Source of the Nile (1805 edition), vol. 3, pp. 287-289
  4. ^ Bruce, p. 289
  5. ^ Bruce, pp. 290-292
  6. ^ Wallis Budge, A history of Ethiopia, page 385
  7. ^ Wallis, 386
  8. ^ Bruce, pp. 292-296
  9. ^ Bruce, pp. 296-300
  10. ^ Bruce, pp. 299f
  11. ^ Bruce, p. 287
  12. ^ (እንግሊዝኛ) Wallis Budge, A History of Ethiopia: Nubia and Abyssinia, 1928 (Oosterhout: Anthropological Publications, 1970), p. 390
  13. ^ (እንግሊዝኛ) Pankhurst, The Ethiopians: A History (Oxford: Blackwell, 2001), p. 107
  14. ^ Bruce, pp. 344-350
  15. ^ Bruce, pp. 381-384
  16. ^ ዋሊስ፣ ገጽ 392
  17. ^ Bruce, pp. 402f
  18. ^ ዋሊስ ገጽ 393
  19. ^ Bruce, pp. 403ff
  20. ^ ዋሊስ፣ ገጽ 395